በዓለም አቀፉ የፖስታ ህብረት (UPU) እና በኢትዮጵያ ፖስታ ትብብር አዘጋጅነት ላለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው እና ኢትዮጵያን የአፍሪካ የፖስታ ጥቅሎች እና የኢ-ንግድ (E-commerce) ዕቃዎች ዋና የሎጅስቲክስ ማዕከል ለማድረግ ያለመው አውደ ጥናት ዛሬ ተጠናቋል፡፡
በማጠቃለያው ላይ የዓለም አቀፉ የፖስታ ህብረት (UPU) ከፍተኛ አመራሮች እና የአፍሪካ ሀገራት የፖስታ ኦፕሬተሮች ተወካዮች በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በኢትዮጵያ ፖስታ ዋና መሥሪያ ቤት ጉብኝት አድርገዋል።
የልኡካን ቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ ፖስታ ሲደርሱ በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በጉብኝቱም ወቅት አባላቱ በኢትዮጵያ ፖስታ የተመለከቱት የዲጂታል አሰራር ሽግግር እና የዘመናዊነት እርምጃዎች እንደተደነቁ እና ጥሩ ተሞክሮዎችን እንደወሰዱ ገልጸዋል።
ይህ አውደ ጥናት በአፍሪካ ደረጃ የፖስታ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አውታርን ለማጠናከር እንዲሁም የሀገራትን ድበር ተሻጋሪ የፖስታ ልውውጥ ለማፋጠን ያለመ ሲሆን፤ በተለይም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የፖስታ ጥቅሎች እና የኢ-ንግድ ዕቃዎች የሎጅስቲክስ ማዕከል የማድረግ ግብን ለማሳካት ከአየር መንገዶች እና ከዓለም አቀፍ የፖስታ አካላት ጋር የሚደረገውን ቅንጅት ያጎለበተ መድረክ ሆኖ አልፏል።













