የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳግማዊ ኃይልዬ ከአለም አቀፍ የፖስታ ህብረት (UPU) የልማት እና ትብብር ዳይሬክተር ከሆኑት ከአቶ ሙቱዋ ሙቱሲ እንዲሁም የአፍሪካ፣ የአነስተኛ እድገት ያላቸው፣ በደሴት ላይ የሚገኙ እና አልሚ ሀገራት አስተባባሪ የሆኑትን አቶ አማዱ አማዱን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት አቶ ሙቱዋ ሙቱሲ እና አቶ አማዱ አማዱ የኢትዮጵያ ፖስታ አጠቃላይ ዕድገት ፣ የአገልግሎት ዘመናዊነትን ለማረጋገጥ እና ቀጠናዊ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አድንቀዋል። አያይዘው እንደገለጹትም የአለም አቀፍ የፖስታ ህብረት የኢትዮጵያ ፖስታን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ለመደገፍ፣ የቴክኒክ እና የአቅም ግንባታ እገዛዎችን ለማድረግ እንዲሁም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና እድሎችን ለመጠቀም በሚደረጉ ጥረቶች ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳግማዊ ኃይልዬ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፖስታ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት፣ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማስፋፋት እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት ለከፍተኛ አመራሮቹ የገለፁ ሲሆን፣ በተለይም የፖስታ ፋይናንስ፣ የኢ-ኮመርስ እና የሎጂስቲክስ መሰረተ ልማቶችን ለማዘመን የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አብራርተዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተቋሙ የጀመራቸውን ግዙፍ የለውጥ እርምጃዎች ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ከአለም አቀፍ የፖስታ ህብረት ጋር ያለው ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እና ሊሰራበት እንደሚገባ በአጽንኦት አሳስበዋል ።









