የኢትዮጵያ ፖስታ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሰረተበትን 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ ያዘጋጃቸውን ልዩ መታሰቢያ ቴምብሮች ቢሾፍቱ በሚገኘው የአየር ኃይል ዋና መሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ በመገኘት በይፋ አስረክቧል።
በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ ፖስታን በመወከል በቦታው ከተገኙት የፊላቴሊ ክፍል ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ገ/ሚካኤል እጅ መታሰቢያ ቴምብሮቹን ተረክበዋል።
የአየር ኃይል ዋና አዛዡ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ አንጋፋው የኢትዮጵያ ፖስታ ለሰራው ሥራ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ተቋሙ የሀገርን ታሪክና ተቋማዊ ቅርስ በፊላቴሊ አማካኝነት አትሞ ለሀገር ውስጥና ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ማድረጉ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በመቀጠልም አቶ ኤርሚያስ ገ/ሚካኤል በስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሀገርን በማስከበርና ድንበር በመጠበቅ ረገድ ላበረከተው ታሪካዊ አስተዋጽኦ እውቅና መስጠት እንደሀገርም ሆነ እንደተቋም ታላቅ ኩራት መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም የተዘጋጁት መታሰቢያ ቴምብሮች የአየር ኃይሉን የ90 ዓመታት የጥንካሬ፣ የዘመናዊነት እና የጀግንነት ጉዞ ለትውልድ የሚያስተላልፉ ዘላቂ ታሪካዊ ሰነዶች መሆናቸውን አብራርተዋል።










