የኢትዮጵያ ፖስታ የ ሳጥን አልባ መልዕክት አገልግሎት እንዲሁም የፖስታ ገበያ መተግበሪያዎችን በስካይ ላይት ሆቴል በይፋ አስመረቀ፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ ያበለጸጋቸውን የ ሳጥን አልባ መልዕክት አገልግሎት እንዲሁም የፖስታ ገበያ መተግበሪያዎችን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የኢትዮጵያ ፖስታ የቦርድ አባላት፣ የኢትዮጵያ ፖስታ ከፍተኛ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች በተገኙበት በስካይ ላይት ሆቴል በይፋ አስመርቋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ ለ132 ዓመታት የቆየውን የታማኝነት አገልግሎቱን ከዘመናዊው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት፣ “ሳጥን አልባ (Virtual)” የመልዕክት አገልግሎት እና “የፖስታ ገበያ” የኢ-ኮሜርስ መተግበሪያዎችን በስካይላይት ሆቴል በደመቀ ሁኔታ አስመርቋል። ይህ ታሪካዊ እመርታ ተቋሙ ከመቶ ዓመታት በላይ እየሰራበት የነበረውን ልምድ ከዘመኑ የፈጠራ ስራዎች ጋር በማዋሃድ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ መፍትሄዎችን ለደንበኞቹ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው።
አዲሱ የቨርቹዋል ፖስታ ሳጥን አገልግሎት የደንበኞችን የሞባይል ስልክ ቁጥር እንደ ዲጂታል አድራሻ እንዲያገለግል የሚያደርግ ሲሆን፣ ይህም ደንበኞች ከየትኛውም የዓለም ክፍል የሚላኩላቸውን መልዕክቶች እና ጥቅሎች በስልካቸው በሚደርሳቸው ፈጣን ማሳወቂያ መከታተል እንዲችሉና ባሉበት ቦታ ሆነው በቤት ለቤት አገልግሎት እንዲረከቡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
በማስጀመሪያ ስነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ሚኒስትር ክቡር አቶ መላኩ አለበል፣ እነዚህ መድረኮች የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ” ስትራቴጂን ወደ ተግባራዊ መፍትሄ የለወጡ ትልቅ ስኬቶች መሆናቸውን ገልጸው፤ በተለይም የፖስታ ገበያ (postGebeya) መተግበሪያ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥሟቸውን የንግድ እንቅፋቶችን በመቀነስ ምርቶቻቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያስተዋውቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትልቅ ዕድል እንደሚከፍት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዳግማዊ ኃይልዬ፤ ተቋሙ በዲጂታል ዘመን ደንበኞችን ከገበያው ጋር ይበልጥ የሚያቀራርብ አዲስ አወቃቀር መከተሉን ገልጸው፣ አዲሱ አሰራር የደንበኞችን ምቾትና እርካታ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር አረጋግጠዋል። በአጠቃላይ ይህ ጅማሬ የኢትዮጵያን የዘመናዊነት ጉዞ የሚያንፀባርቅና በሀገር ውስጥ የሚላኩ ዶክመንቶችንም ሆነ ጥቅል መልዕክቶችን በቴክኖሎጂ የታገዘና የተሳለጠ እንዲሆኑ የሚያደርግ ግዙፍ እርምጃ ነው።
በስነስርአቱ ላይ የተገኙ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ባለቤቶችም ይህ የፖስታ ገበያ መተግበሪያ መፈጠሩ ምርቶቻቸውን በመላው ዓለም ለሚገኙ ደንበኞች እንዲያደርሱ እና በግብይት ልምዳቸውም በብዙ መልኩ ከፍ ያለ ለውጥ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡





















