ኢትዮጵያን የአፍሪካ የፖስታ ጥቅሎች እና የኢ-ንግድ ዕቃዎች የሎጅስቲክስ ማዕከል ለማድረግ ያለመው ታላቅ አህጉራዊ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ!

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የፖስታ ጥቅሎች እና የኢ-ንግድ ዕቃዎች የሎጅስቲክስ ማዕከል ለማድረግ ያለመው ታላቅ አህጉራዊ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ!

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ — በዓለም አቀፉ የፖስታ ህብረት (UPU) እና በኢትዮጵያ ፖስታ ትብብር የተዘጋጀው “የአፍሪካ ቀጠናዊ የትራንስፖርት አውደ ጥናት” (Regional Transport Workshop for Africa) ዛሬ ነሐሴ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በይፋ ተከፈተ። ይህ ታላቅ መድረክ በአፍሪካ የሚገኙ የፖስታ ኦፕሬተሮች አመራሮችን እና በአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካዮችን ጨምሮ የንግድ እና የአህጉራዊ ትስስር ቁልፍ ተዋናዮችን በአንድ ያሰባሰበ ነው።

ይህ አውደ ጥናት ሶስት ግዙፍ ተቋማትን ያገናኘ ነው፦ በ1874 እ.ኤ.አ. የተመሰረተና የ192 አባል ሀገራትን ኔትዎርክ በማስተባበር ዓለም አቀፍ የፖስታ ህጎችንና ትብብርን የሚመራው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ኤጀንሲ የሆነው ዓለም አቀፉ የፖስታ ህብረት (UPU)፣ በኢ-ኮሜርስ እና ፈጣን ጥቅሎች የመጨረሻ መዳረሻ አገልግሎት አቅራቢ (Last-Mile delivery service provider) የሆነውና ራሱን በከፍተኛ ደረጃ እያዘመነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፖስታ፣ እንዲሁም በአፍሪካ ትልቁ እና በዓለም አቀፍ የካርጎ ሎጅስቲክስ አቅሙ በስፋት የሚታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ናቸው።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የፖስታ ተቋማት ተወካዮች፣ የአቪዬሽን ዘርፍ ባለሙያዎች እና የሎጅስቲክስ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ውይይቶቹ የአፍሪካን የፖስታ እና ኢ-ንግድ ዕቃዎች ትራንስፖርት እና የአቅርቦት ሰንሰለት መሠረተ-ልማት ማዘመን ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ በተለይም በአየር ካርጎ ሎጅስቲክስ እና በመሬት ላይ ስርጭት መካከል ያለውን ቅንጅት በማጠናከር ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥን ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ ያለመ ነው። እንደዚሁም ይህ አውደ ጥናት በአህጉራችን አፍሪካ የሚገኙ የቀጠናዊ ትስስሮችን ማሳደግ እንዲሁም በፖስታ ቅብብሎሽ ሰንሰለት እና የመልዕክት ደህንነት ረገድ ተፎካካሪነትን ማጎልበት ላይ ትኩረቱን አድርጓል። በተጨማሪም ይኸው መድረክ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የትራንስፖርት ህብረት በጠንካራ መሰረት ላይ በመትከል፣ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳግማዊ ኃይልዬ፣ የፖስታው ዘርፍ እያደረገ ያለውን ስትራቴጂያዊ የለውጥ ጉዞ በማንሳት፤ አባል ሀገራት ዘመናዊ የኢ-ኮሜርስ እና የመጨረሻ ማይል የዕቃ አቅርቦት ቴክኖሎጂዎችን በማስተሳሰር ለተገልጋዮች የላቀ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተዋል። በመድረኩም የፖስታ አገልግሎት ከተራ የደብዳቤ ልውውጥ አልፎ ለአህጉሪቱ ንግድ፣ ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዞችና ለድንበር ተሻጋሪ ኢ-ኮሜርስ ዋነኛ የሎጂስቲክስ ሞተር መሆኑ ጎልቶ ተነስቷል። በተመሳሳይ የዓለም አቀፉ የፖስታ ህብረት (UPU) የልማት እና ትብብር ዳይሬክተር ሚስተር ሙቱዋ ሙቱሲ፣ አውደ ጥናቱ አፍሪካ በቀጠናዊ ንግድ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። አያይዘውም፣ ኢትዮጵያ ፖስታ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላስመዘገበው ስኬትና ሽልማት አድናቆታቸውን ገልጸው፤ የተቋሙ ስኬታማ የለውጥ ጉዞ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርዓያ መሆኑን አብራርተዋል።

ከፖስታ አገልግሎት መሻሻል ባሻገር፣ የዚህ ስትራቴጂያዊ መድረክ ዋነኛ ዓላማ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቀዳሚ የሎጅስቲክስ ማዕከል (Logistics Hub) አድርጎ መገንባት ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለውን ሰፊ ዓለም አቀፋዊ የአየር ትስስር ከኢትዮጵያ ፖስታ ሀገር አቀፍ እና ቀጠናዊ የቅርንጫፍ ኔትዎርክ ጋር በማስተሳሰር፤ ኢትዮጵያ የአህጉሪቱን የኢ-ኮሜርስ ዕድገት ለመምራት እና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠናን ተግባራዊነት ለማሳለጥ ምቹ ቁመና ላይ እንደምትገኝ አውደ ጥናቱ አጉልቶ ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል።

መድረኩ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ በተግባራዊ ጉብኝት የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ግዙፍ የካርጎ ማዕከል እና የኢትዮጵያ ፖስታን ዓለም አቀፍ የፖስታ ልውውጥ ማዕከል በመጎብኘት፤ ኢትዮጵያ ለወደፊቱ የአፍሪካ ሎጅስቲክስ ዘርፍ የዘረጋችውን የተቀናጀ መሠረተ-ልማት በአካል የሚመለከቱ ይሆናል።

More updates Ethiopost

News

የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ፖስታ የቦርድ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ሐና አርዓያሥላሴ ወደ ታሪካዊው አራዳ ፖስታ ቤት የተዘዋወረውን እንዲሁም በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቆ ሥራ የጀመረውን  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፖስታ ሙዚየም ጎበኙ።

በጉብኝታቸው ወቅት ለ50 ዓመታት በዋናው መሥሪያ ቤት ተጠብቀው ቆይተው በዘመናዊ መልክ የተደራጁ ብርቅዬ ቴምብሮችንና ታሪካዊ የፖስታ ቅርሶችን በመመልከት በአደረጃጀቱ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል።

Read More »
News

የኢትዮጵያ ፖስታ በፖስታ እና ሎጅስቲክስ ዘርፍ ላለፉት አምስት ዓመታት ላመጣው የዲጂታል ሽግግር ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር (MInT) የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተበረከተለት!

ዕውቅናው የተገኘው ብሔራዊ መታወቂያን ከአገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር፣ መልእክቶችን በቀጥታ (Real-time) መከታተል የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት እና አጠቃላይ የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በማዘመን በተመዘገቡ ስኬቶች ነው።

Read More »
News

ለኢትዮጵያ ፖስታ አመራሮችና ሠራተኞች ሲሰጥ የቆየው ባለሁለት ዙር የሞጁላር የግብር ሕግና አሰራር ስልጠና ተጠናቀቀ::

ስልጠናው በተለይም ከቅጥር የሚገኝ ገቢ፣ የወጪ መጋራት እና ሌሎች መሠረታዊ የታክስ አሰራሮች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር እንዲለውጡ ተሳስቧል።

Read More »
News

በUPU እና በኢትዮጵያ ፖስታ አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ቀጠናዊ የፖስታ ትራንስፖርት አውደ ጥናት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ፡፡ 

መድረኩ የአህጉሪቱን የፖስታ እና የኢ-ንግድ ዕቃዎች ትራንስፖርት እንዲሁም የሎጂስቲክስ አቅርቦት ሰንሰለት በማዘመን ረገድ ቀጠናዊ ትብብርን ለማጠናከር አስችሏል።

Read More »