በውይይቱ መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ፖስታ የአቅርቦት እና ፋሲሊቲ ቺፍ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ጋሻው መርሻ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፤ አያይዘውም በ2017 በጀት ዓመት ለነበረው አፈጻጸም ሁሉም የኢትዮጵያ ፖስታ ሰራተኛ ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ አንስተው በቀጣይም ይኸው የሥራ መነሳሳት እና ተልዕኮዎቻችንን በድል የመወጣት ባሕል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በውይይቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በአምስቱ ዋና ዋና የስትራቴጂክ ምሰሶዎችን መሰረት ባደረጉ አፈጻጸሞች እና ቀጣይ እቅዶች ላይ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በሰው ሀብት አስተዳደር ዙርያ የሚኖሩ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችም እንዲሁ ሰፊ ገለጻ ተደርጎባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳግማዊ ኃይልዬ በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ ከሰራተኞች ለተነሱት አጠቃላይ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሾችን የሰጡ ሲሆን በውይይቱ መጠናቀቂያም ድርጅቱ እያስመዘገበ ላለው ዘርፈ ብዙ ስኬት ዋና ባለቤት ሰራተኛው መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉን አቀፍ እድገት ለማስመዝገብ እየተሰራ እንደሆነ እና የቀጣይ በጀት ዓመት ግቦችን በጋራ ለማሳካት የሁሉም ሰራተኞች አስተዋጾ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡