የኢትዮጵያ ፖስታ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘመናዊና ሁሉን አቀፍ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ያቀደውን አዲሱን የፖስት ፋይናንስ አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ በጥራትና በብቃት ለመተግበር በሁሉም ዲስትሪክቶች ለሚገኙ የዲስትሪክት አመራሮች እና ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየውን አጠቃላይ የስልጠና መርሃ-ግብር አጠናቋል።
በመዝጊያ ስነ-ሰርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፖስታ ቺፍ ኮሜርሻል ኦፊሰር ወ/ሮ ትዕግሥት በቀለ በንግግራቸው፤ ሁሉም ተሳታፊዎች ስልጠናውን ወዳሉበት ዲስትሪክት በመውሰድ ትልቅ ውጤት እንዲያመጡ አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።
ለሁሉም የስልጠናው ተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት የተበረከተ ሲሆን የተማሩትን እውቀት ወደ መሬት በማውረድ አገልግሎቱን ፈጥኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ፖስታም ይህ ስልጠና መጠናቀቁን ተከትሎ አዲሱን የፖስት ፋይናንስ አገልግሎት በሙሉ አቅም ወደ ህብረተሰቡ በማድረስ በይፋ ለደንበኞቹ ዘመናዊና የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።













