በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮጵያ ፖስታ ለኢ-ኮሜርስ ሥራ እያደረገ ያለውን ዝግጁነት እና የተለያዩ የሥራ ክፍሎችን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባውን የኢ-ኮሜርስ መተግበሪያ ጨምሮ በቀጣይ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎቱን በተሻለ ለማዘመን እየሰራቸው ባሉ ሥራዎች ዙሪያ በዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ዳግማዊ ኃይልዬ እና በድርጅቱ አመራሮች ለኮሚቴው ገለጻ ተደርጓል፡፡
በተመሳሳይ በውይይቱ ላይም የኢትዮጵያ ፖስታ ኢ-ኮሜርስ መተግበሪያ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ምርቶችን ለዓለም አቀፍ ገበያ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ እና የንግድ ስርዓቱንም በማዘመን ሂደት ትልቅ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው የተነሳ ሲሆን፤ ኮሚቴው አጠቃላይ የንግድ ምህዳሩን ለኢ-ኮሜርስ ምቹ ከማድረግ አንጻር መሰራት በሚገባቸው ሥራዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በመጨረሻም በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ይድነቃቸው ወልደተንሳይ እንዲሁም የኮሚቴው አባላት በጉብኝታቸው የተመለከቱት የኢትዮጵያ ፖስታ የኢ-ኮሜርስ ሥራ ዝግጅት አበረታች መሆኑን ገልጸው ተጠናክሮ መቀጠልና በሌሎች የሀገሪቷ አካባቢዎችም በተመሳሳይ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት አንስተዋል፡፡














