ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ፖስታ ዋና መሥሪያ ቤት ለ3ኛ ጊዜ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ “የተከፋፈለችውን ዓለም የሚያስተሳስሩ ሙዚየሞች” በሚል እጅግ ወቅታዊ መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፖስታ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ በረከት ዘውዴ እና የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በክበረ በዓሉ ላይ “የፖስታ አገልግሎት ከቀላል የመልዕክት መለዋወጫነት ባሻገር የሀገርን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ትረካዎች የሰነደ ታሪካዊ አምባሳደር መሆኑ የተነሳ ሲሆን” በዚህ ፈታኝና በተከፋፈለ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ ሙዚየሞች የሀገሪቱን ዘመናዊነት፣ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና የጋራ እሴቶችን በማጉላት ሕዝቦችን የማገናኘት ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ተገልጿል፡፡
በመቀጠልም በዕለቱ የኢትዮጵያ ፖስታ ሙዚየም በሙዚየም ብቃት ማረጋገጫ ደረጃዎች ተገምግሞ የሰርተፊኬት ሽልማት የተበረከተለት ሲሆን የእውቅናውን ሰርተፊኬት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ በረከት ዘውዴ ለኢትዮጵያ ፖስታአስረክበዋል፡፡
በዚህም ተቋሙ የሀገርን ቅርስ በአግባቡ ጠብቆ ለማቆየትና ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ እያደረገ ላለው ቁርጠኝነት የተሰጠ ትልቅ ማረጋገጫ ነው ተብሏል።





