በቻይና ፖስታ ቢሮ (SPB) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሊዮ ጂንሮንግ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ዛሬ ከኢትዮጵያ ፖስታ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር የሥራ ውይይት እና የመስክ ጉብኝት አካሂደዋል።
የዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ እና የኢትዮጵያ ፖስታ ቺፍ ኮሜርሻል ኦፊሰር ወ/ሮ ትዕግስት በቀለ ከሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ልዑካን ቡድኑን በኢትዮጵያ ፖስታ ዋና መ/ቤት አቀባበል አድርገውላቸዋል። በቆይታቸውም ለልዑካን ቡድኑ የተቋሙን አጠቃላይ ገጽታ እና በጋራ መሥራት የሚያስችሉ ቁልፍ መስኮችን የተመለከተ ገለጻ ቀርቦላቸዋል።
በገለጻውም የኢትዮጵያ ፖስታ የዓመታት ታሪካዊ ተአማኒነት፣ ያሉት ከ1,800 በላይ ቅርንጫፎች እና ከ190 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር አዲስ አበባን የምሥራቅ አፍሪካ የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም መሆናቸው ተመላክቷል። በተጨማሪም የዲጂታል አሠራሮችን በአጋርነት የመጠቀም አቅም በተቋሙ መጎልበቱ ከቻይና ፖስታ ቢሮ ጋር ስትራቴጂካዊ ትብብር ለመፍጠር ቁልፍ መንገዶች መሆናቸው ተገልጿል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት በፖስታ ዘርፉ የአቅም ግንባታ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከተወያዩ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ፖስታን አጠቃላይ የኦፕሬሽን አሠራር ሂደት ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ ከፍተኛ ልዑካኑ በኢትዮጵያ ፖስታ እየተከናወኑ ባሉ የዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለውጦች መደሰታቸውን ገልጸው፤ በሁለቱ ሀገራት ተቋማት መካከል ያለውን የልምድ ልውውጥና የአቅም ግንባታ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቻይና ፖስታ ቢሮ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሊዮ ጂንሮንግ የተመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ፖስታ የሥራ ውይይት እና ጉብኝት አደረገ፡፡
በውይይቱ የኢትዮጵያ ፖስታ ያለውን ሰፊ መሠረተ ልማትና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለውን አጋርነት በመጠቀም አዲስ አበባን የምሥራቅ አፍሪካ የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ለማድረግና በዲጂታል አሠራርና በአቅም ግንባታ በጋራ ለመሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ተደርሷል።












