የኢትዮጵያ ፖስታ የላቀ የካርታ ውህደት እና የሳተላይት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሎጀስቲክስ ምህዳሩን ለማዘመን ያስችለዉ ዘንድ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። ይህ አጋርነት ዘመናዊ የካርታ አሰራርን በኢትዮጵያ ፖስታ ሎጅስቲክስ ማዕቀፍ ውስጥ በማካተት የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን እና ጥራትን ለማሳደግ ያለመ ነው:: ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ፈጣን እና አስተማማኝ የቤት ለቤት እደላ አገልግሎትን በማሳለጥ የደንበኞችን እርካታን ማሻሻል ይቻላል።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ስራ አስፈፃሚ የተከበሩ አቶ ዳግማዊ ኃይልዬ እንደገለጹት ይህ ትብብር የፖስታ አገልግሎትን የሚያዘምንና የኢትዮጵያ ፖስታ የሎጂስቲክስ ስራዎችን የሚለውጥ ነዉ ። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ አብዲሳ ይልማ የስፔስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፈጠራን እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማስፋፋት ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ አመልክተዋል። ይህ ትብብር እያደገ የመጣውን የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት እና በሎጂስቲክስ ዘርፍ መሪ ሆኖ ለመቀጠል ጉልህ አበርክቶት ያለው ነው።