የኢትዮጵያ ፖስታ እና የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሀገሪቱን የግብይት እና የሎጀስቲክስ ሰንሰለት በማቀናጀት ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።
የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱን የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳግማዊ ኃይልዬ እና የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ በኃይሉ ንጉሴ ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንን ዘርፈ ብዙ የእህል፣ የጥራጥሬ እና የአትክልት ምርቶች ለህብረተሰቡ በስፋት ለማድረስ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳግማዊ ኃይልዬ የኢትዮጵያ ፖስታ ያለውን ግዙፍ የሎጀስቲክስ አቅም፣ የትራንስፖርት መዋቅር እና በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን ተደራሽነት በመጠቀም ምርቶቹ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ዜጎች እንዲቀርቡ እንደሚደረግ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ በኃይሉ ንጉሴ በበኩላቸው ይህ ስምምነት ምርቶችን በቀጥታ ከምንጩ (ከገበሬው) ወደ ሸማቹ በማድረስ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጡም በላይ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ከሀገራዊ ፋይዳ አንጻር ይህ ጥምረት መንግስት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሠራቸው ለሚገኙ ሥራዎች በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዝ ነው።















