በሻንጋይ የተካሄደው የ2024 የኤዥያ አለም አቀፍ የቴምብር ኤግዚቢሽን የእስያን ባህል በፊላቴሊ ጥበብ የሚያሳይ ደማቅ በዓል ነበር። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች አስደናቂውን የቴምብር ማሳያ አድንቀዋል፣ እያንዳንዱም የቴምብር ስራዎች ታሪክን፣ ጥበብን እና ወግን ይናገራሉ።
ይህ በአይነቱ ልዩ በሆነውን የቴምብር ኤግዚቢሽን የዓለም የፊላቴሊ ልማት ማህበር (WADP) በፊላቴሊ ፈጠራ ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ እና አውደ ጥናት አዘጋጅቷል። የኢትዮጵያ ፖስታ በዚሁ ዝግጅት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የፊላቴሊ ማዘመኛ መንገዶችን ለመቀየስ የሚረዳውን ልምድና እውቀት አግኝቷል።
ይህንንም ተከትሎ ቴክኖሎጂንና አዳዲስ አቀራረቦችን በመከተል የኢትዮጵያን ባህላዊ ቅርሶችንና ትውፊቶችን እንዲሁም ሀገራዊ ታላላቅ ኩነቶችን በፊላቴሊ ዘርፍ ለዓለም የማስተዋወቁን ተግባር የኢትዮጵያ ፖስታ አጠናክሮ ይቀጥላል።